"የትም አገር ልኑር ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ኢትዮጵያዊነት ከደም የሚወጣ አይደለም" ድምፃዊ ኤልያስ "ኪዊ" የማነ

Elias Kiwi USA.jpg

Singer Elias "Kiwi" Yemane. Credit: E.Yemane

Get the SBS Audio app

Other ways to listen

ድምፃዊ ኤሊያስ "ኪዊ የማነ፤ የሙዚቃ ሕይወት ጉዞ ከቀበሌ ተንስቶ የምሽት ክለብ መድረኮች ላይ አላከተመም። ከቶውንም በጦር ትምህርት ቤት ሁርሶ፣ በስደት ሞቃዲሾ፣ በዳግም ሠፈራ ኒውዝላንድና አውስትራሊያ የጥበብ ሙያው እስትንፋስ ሆኖ ዛሬም ድረስ አለ።


ኒውዝላንድ

ድምፃዊ ኤሊያስ በሶማሊያ የእርስ በእርስ ጦርነት ሳቢያ ሁለተኛ የስደት መጠለያው የሆነችው የኬንያን የስደተኛ ካምፖች አፈራርቆ ቆይቶባቸዋል።

ጥቂት ቆይቶ ግና የሕይወት ኮከቡ አቅጣጫ ወደ ኒውዝላንድ አመራ።

ሕይወቱን ሙጥኝ ያለችውን አገርኛ ሙዚቃ ከምዕራቡ ዓለም የሁለት ዓመታት የሙዚቃ ክህሎተ ትምህርት ጋር አዋደዳት።

"አፍሮ-ኪዊ" ባንድን መሠረተ።

በተለያዩ የኒውዝላንድ ከተሞች እየተዘዋወረም የጥበብ ውጤቶቹን ማቅረብ ቀጠለ።

እንዲያ ሳለ፤ በዓለም የፖፕ ሙዚቃ ንጉሥነት የተሰየመው ማይክል ጃክሰን ታላቅ የሙዚቃ ድግሱን ይዞ ከኒውዝላንድ ሰሜናዊ ደሴት ታላቋ ከተማ ኦክላንድ ገባ።

ኤልያስ፤ በትናንት አስከፊ የኢትዮጵያ ረሃብ ምልሰታዊ ምልከታ "Live Aid Band - We Are The World" ሕብረ ዝማሬና በኦክላንድ አፍላ የሙዚቃ ድግስ ዝንቅ ስሜቶች መካከል የማይክል ምስል ገዝፎ አዕምሮው ውስጥ ተደቀነ።

አንድ ዕሳቤ ተጫረለት።

ስጦታ ለማይክል ጃክሰን

ሁለት ስጦታዎቹን በአንድ ጥቅል ሸክፎ ማይክል ጃክሰን ወደ አረፈበት ሆቴል አመርቶ ከማይክል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጋር ተገናኘ።

ሃሳቡን አስረድቶ ስጦታውን አበረከተ።

ስጦታዎቹ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን ከዓመታት በፊት በ "13 የፀሐይ ወራት" ፀጋነት ኢትዮጵያን ያስተዋውቅባት ከነበሩት የማስታወቂያ ግፀታዎች አንዲቱ የነበረችውን "ውቢት ኢትዮጵያ" አልማዝ አመንሲሳ ምስልና "የእንጨት ሚዶ" ነበሩ።
Tourism.jpg
Almaz Amensisa "Beautiful Ethiopia". Credit: Ethiopian Tourism Commission

ድምፃዊ ኤሊያስ ውለታ ከሚገባቸውና ውለታ መላሽም ከሆኑት ኢትዮጵያውያን አንዱ ነበርና።

የሙዚቃ አልበም

ኔውዝላንድ ውስጥ ከ16 አገራት የተውጣጡ ድምፃውያን የሙዚቃ ስብስብ ሥራዎች ተቀርፀው ገበያ ላይ ሲውሉ አንዱ ነጠላ ዘፈን የኤልያስ ነበር።

ከእዚያም ባገኘው ገቢ የእራሱን አንድ አልበም "አዲስ" በሚል መጠሪያ የዘፈን ስብስቦቹን አቀረበ።

ያም ለ "Good Morning New Zealand" የቴሌቪዥን እንግድነት አበቃው።

ሲልም፤ አውስትራሊያ በየዓመቱ በሚካሔደው "WOMAdelaide" ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ እንዲሳተፍ ተጋበዘ።

በኢትዮጵያውያን ዘመናዊና የአገር ባሕል የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች ታጅቦ ከታላላቅ የዓለማችን ሙዚቀኞች ጋር መድረክ ተጋራ።

የአደላይድ መድረክ የአውስትራሊያ ዕጣ ፈንታውን አሰመረች።

አውስትራሊያ መድረኳን ብቻ ሳይሆን የሴት ልጇን ፍቅርም አክላ ሰጥታ ለላስ ቬጋስ ፈጣን ሙሽርናም አበቃችው።

በአገረ አሜሪካ አዲሱን የጋብቻ ሕይወት ብቻም ሳይሆን ሲያጣጥም የነበረው ከዝነኛዎቹ ቴዎድሮስ ታደሠና ቴዲ አፍሮም ጋር መድረክና ምክር ተጋርቷል።

ስለ ዕውቁ የሙዚቃ አቀናባሪ ኤ፤ኢያስ መልካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማው ከቴዲ አፍሮ አንደበት ነበር።

ከሁለት ዓመታት በኋላም አገር ቤት ሔዶ ሳለ ከቶውንም "በቃኝ" የሚለውን የሙዚቃ ሥራውን ከኤሊያስ መልካ ጋር አንድ ላይ አቀናብረው ለማስቀረፅ በቃ።

ኤሊያስ አሁንም ድረስ ነዋሪነቱ አውስትራሊያ ውስጥ ቢሆንም፤ ሁለት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆቹን "ባሕላዊ ዕሴቶቻቸውንና ማንነታቸው ጠብቀው እንዲያድጉ" በሚል ዕሳቤ ለ18 ዓመታት ያሳደገው አገር ቤት ነው።

የጥወራ ዘመኑን ማሳለፍ የሚሻውም በአገረ ኢትዮጵያ ነው።

Share