የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሕፃን ሔቨንን የይግባኝ መነሻና ሂደት አስመልክቶ መግለጫ ሰጠ

"ለመረጃ ይኾነን ዘንድ፣ ድጋፋችሁም መረጃን መሠረት አድርጎ፣ ዕውነትን በአረጋገጠ፣ ሕግን በጠበቀ ሁኔታ እንዲሰነዘር ፍላጎታችን መኾኑን በማመን በአማራ ክልል ፍትሕ ተቋማት ይህንን አሰቃቂ የወንጀል ድርጊት ተከትሎ ምን ተደረገ፣ ጉዳዩስ ምን ላይ ነው የሚለውን በተመለከተ አጭር መረጃ እንደሚከተለው መስጠት አስፈልጓል" - የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ

AJB and Heavean.jpg

Heaven (R). Credit: PD

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ሕፃን ሔቨን ላይ የደረሰውን አሰቃቂ የሞት ክስተት፣ ክስ፣ የፍርድ ቤት ብይንና የይግባኝ ጥያቄ አስመልክቶ ዜጎች ሂደቱን እንዲረዱ ለግንዛቤ ማስጨበጫነት ይረዳል ያለውን መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫውም የሚከተለውን ማብራሪያ አስፍሯል፤

ድርጊቱ የተፈጸመው ሐምሌ 25/2015 ዓ.ም ነው፡፡ የድርጊቱ ቦታ ቀበሌ 14 ተብሎ ይጠራ ከነበረው አካባቢ ሲኾን ወቅቱ ሰላም የጠፋበት፣ መረጋጋት የሌለበት፣ ከፍተኛ በጦር መሳሪያ የተደገፈ ግጭት (ጦርነት) የነበረበት ወቅት ነው፡፡

ይህ ወቅት ብዙ ወንጀለኞች ግጭቱን እንደሽፋን በመቁጠር ብዙ ወንጀል ፈጽመውበታል፣ እራሳቸውን በግጭቱ ሸፍነው ብዙ አድርገዋል፡፡

በዚህ ወቅትም ልጃችን ሄቨን አንዷ የእነዚህ ግጭቱ ዕድል ለፈጠረለት ሰው ተጠቂ ኾናለች፡፡ ሕጻኗ ምን ኾነች፣ እንዴት ተገኘች፣ የት ተገኘች፣ ጉዳዩ ወደ ሕግ ቦታ እንዴት መጣ ሕጻኗ የተገኘችው ሻወር ቤት ውስጥ ነው፣ ስትገኝም ሕይወት ነበራት በሚባል ሁኔታ ላይ አይደለም፡፡

 ፖሊስም ባለበት ከቦታው ወደ ሆስፒታል (መጀመሪያ የግል ጤና ተቋም)፣ ቀጥሎም የመንግሥት ሪፈራል ሆስፒታል ተወስዳለች፡፡ ሁለት ቦታ ምርመራ ተሠርቷል፡፡

 ፖሊስ አብሮ በሂደቱ እና ሂደቱንም እየተከታተለ ስለነበር እና ሕጻኗ በተገኝችበት ቤት ሌላ ሰው አለመኖሩ ሲረጋገጥ ጥርጣሬውን ቤት ውስጥ ከነበረ ሰው ጋር አድርጎ ምርመራውን ቀጥሏል፡፡ በመኾኑም ይህ ፍርደኛ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል፡፡

 በምርመራው የአካባቢ ምስክር ድርጊቱን ያዬ ባለመኖሩ በቤት ውስጥ ሌላ ሰው አለመኖሩን እና በሕጻኗ አካል ላይ የደረሰውን ጉዳት የሕክምና ምርመራውን መሠረት አድርጎ ተካሂዷል፣ (ከ27 ጀምሮ በተለይ ባሕርዳር ከተማ ከፍተኛ ብጥብጥ እና ግጭት በመኖሩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበረው የአሁኑ ፍርደኛ ወጥቶ ነበር)፡፡

 ከተማው ተረጋግቶ በቁጥጥር እስኪውልም በነጻነት ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ (የህግ አስፈፃሚዎችም ሲስተር አበቅየለሽም በዚህ ሂደት ለጥቃት ተጋላጭ ነበሩ)፡፡

ስለሆነም በአስቸጋሪ ወቅት ግጭት በነበረበት ወቅት ሐምሌ 25/11/2015 ዓ.ም ጥቃት ተፈጽሟል፡፡

 በፍትሕ ተቋማቱ (በፖሊስ፣ በጠቅላይ አቃቢ ሕግ እና በፍርድ ቤት ምን ተከናወነ ? )

1.ምንም እንኳ ወቅቱ አስቸጋሪ ቢኾንም የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቶ ተጠርጣሪው ወዲያው በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

 2.ፖሊስ ጣቢያው በታጠቁ ኃይሎች ሲሰበር እና ሲዘረፍ መውጣቱን እና የተጎጅ ቤተሰብን፣ የሕግ አካላትን ሳይቀር ተጽዕኖ ለማድረስ ቢሞክርም ተመልሶ በፖሊስ ኃይል ለሕግ ቀርቧል፣ በቁጥጥር ስርም ውሏል፡፡

3.ምርመራው ተደርጎ በምርመራው እና ባሉት የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች መነሻነት ፍትሕን ለማረጋገጥ በሚያስችል ሁኔታ የሀገሪቱ አግባብ የኾነውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ ተጠቅሶ ከፍተኛ ቅጣት በተደራራቢ ወንጀል ሁለት ክስ ማቅረብ ተችሏል፡፡

4.ክሶችም የግፍ ግድያ የወንጀል ሕጉ 539 እና በመድፈር መግደልን 620 (3) ያጣቀሰ ነበር፡፡ ይህም የሞት ፍርድ ወይም የዕድሜ ልክ እስራት ድረስ የሚያስቀጣ ነው፡፡

5.በክርክር ሂደት ተከሳሽ ክዶ ጠበቃ አቁሞ የተከራከረ ሲኾን ይህም ሕጋዊ አሠራር ነው፤ በክርክሩ የታዩ የሙያ ሥነ ምግባር ጉዳዮች ወይም ወንጀል ከተፈጸመ ማየቱ እና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደተጠበቀ ኾኖ፡፡

6.መጨረሻ ግራ ቀኝ ክርክሩን ሰምቶ የቀረበው ማስረጃ የግፍ ግድያን ሳይኾን (539) በመደፈር መሞቷን የሚያረጋግጥ መኾኑን በማረጋገጥ ተጠርጣሪው በ25 ዓመት ፅኑ እስራት ሊቀጣ ውሳኔ አርፎበታል፡፡ ስለኾነም ፍርደኛው አሁንም ማረሚያ ቤት ይገኛል፡፡

7.በአሁኑ ወቅት ፍርደኛው የፍርደኛ ይግባኝ አቅርቦ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በመመርመር ላይ ይገኛል፣ ይሄም ሕጋዊ እና የተለመደ አሠራር ነው፡፡ ዐቃቢ ሕግ የስር ፍርድ ቤት የወሰነው የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ በሕጉ አግባብ መኾኑን ቢያንሰው እንጂ የሚበዛበት አለመኾኑን ከወንጀሉ አሰቃቂነት አኳያ በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ፊት ቀርቦ አስረድቷል፡፡ ጉዳዩም ለውሳኔ ለሚቀጥለው ዓመት ተቀጥሮ አድሯል፡፡ አሁንም ፍትሕ ቢሮው ጉዳዩን በአግባቡ እየተከታተለው ይገኛል፡፡ ምናልባት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ውሳኔ በአሉታዊ ቢኾን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በዐቃቢ ሕግ በኩል የሚቀርብ እንደኾነም ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡

እንደመውጫ፡-

በሕጻናት ላይ የሚፈፀም ወንጀል በሀገር ላይ፣ በትውልድ ቀጣይነት ላይ፣ ሕግን ብቻ ሳይኾን ሰው መኾንን የተቃረነ አውሬነት መኾኑን አውቀን ልንዋጋው፣ ልናስቆመው የሚገባ ነው፡፡ ሕግን ብቻ ሳይኾን ፍትሕን፣ እኩልነትን፣ ሞራልን፣ ርትዕን በአጠቃላይ የተቃረነ ፀያፍ ወንጀል ሲኾን ሁላችንም በአንድነት በቅንጅት በእኩል ተቆርቋሪነት ልንታገለው ይገባል፡፡ ወደፊት የሕግ ማሻሻያ ሥራዎችንም ታሳቢ አድርገን ድምፃችንን ለመስጠት ዕድሉ አለ፡፡ በዲስፕሊን የሚታዩ ጉዳዮች፣ በወንጀል የሚያስጠይቅ በሂደቱ የተንፀባረቁ ጉዳዮች ካሉ በጥሞና (በጥቆማችሁ መነሻነት) ይታያሉ፡፡ ለሕግ፣ ለፍትሕ፣ ለርትዕ እንሠራለን!

 ነፍስሽ ትረፍ ህጻን ሄቨን!!!

በቃ ይበለን!

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም




Share
Published 20 August 2024 9:04pm
By Stringer Report
Source: SBS

Share this with family and friends