የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሕወሓት በልዩ ሁኔታ የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ሰጠ

በፓሪስ ኦሎምፒክ የሜዳል ሠንጠረዥ አውስትራሊያ ሶስተኛ ኢትዮጵያ 68ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ

Amharic News Flash 2024.jpg

Credit: SBS Amharic

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 3 ቀን 2016 ባወጣው መግለጫ ለሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የሰጠ መሆኑን አስታወቀ።

ቦርዱ ከሕጋዊ ሰውነት ማላበሻው ውሳኔ ላይ የደረሰውም ሕወሓት ሐምሌ 19 ቀን 2016 ያቀረበውን የሕጋዊ ሰውነት ጥያቄ ደብዳቤና የማሻሻያ ዐዋጁን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒስቴር ሕወሓት ሕገ መንግሥታዊና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱን በመግለጡ በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገብ ተደርጓል ሲል አመላክቷል።
TPLF.png
Credit: NEBE
አክሎም፤ የፖለቲካ ድርጅቱ በልዩ ሁኔታ ስለመመዝገቡ ሲያስረዳም "የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ በዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 ላይ በተደነገገው መሠረት በልዩ ሁኔታ የሚል ቃል ያለበት ሆኖ እንዲዘጋጅ ቦርዱ ወስኗል" ብሏል።

ሕወሓት በልዩ ሁኔታ የመመዝገብ ውሳኔን የያዘው የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ከደረሰው ዕለት አንስቶ ባሉት ስድስት ወራት የቦርዱ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ በማድረግ መተዳደያ ደንቡን አስፀድቆ፤ አመራር አባላቱን የሚያስመርጥ ይሆናል።

ፓሪስ ኦሎምፒክ 2024

ከጁላይ 26 / ሐምሌ 19 አንስቶ ፍፃሜው እሑድ ነሐሴ 5 / ኦገስት 11 በሚሆነው የፓሪስ ኦሎምፒክ 2024 ተወዳዳሪ ከሆኑ 184 ሀገራት ውስጥ 80ዎቹ በተወዳደሩባቸው 32 የስፖርት ዘርፎች ድል በመንሳት ከወርቅ እስከ ነሐስ ያሉ ሜዳሎችን ለመሸለም በቅተዋል።

እስከ ፓሪስ ኦሎፒክ 2024 ፍፃሜ ዋዜማ ድረስ፤
  • ዩናይትድ ስቴትስ፤ 33 ወርቅ 39 ብር 39 ነሐስ በድምሩ 111 ሜዳሎችን በማግኘት 1ኛ
  • ቻይና፤ 33 ወርቅ 27 ብር 23 ነሐስ በድምሩ 83 ሜዳሎችን በማግኘት 2ኛ
  • አውስትራሊያ፤ 18 ወርቅ 16 ብር 14 ነሐስ በድምሩ 48 ሜዳሎችን በማግኘት 3ኛ
  • ኢትዮጵያ 2 የብር ሜዳሎችን በማግኘት 68ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

Share
Published 10 August 2024 12:31pm
By Stringer Report
Source: SBS

Share this with family and friends