'ለውጥ ከአሁን አንስቶ ይጀምራል' በእንግሊዝ ሌበር ፓርቲ አሸናፊነት፤ ኪር ስታርመር ለጠቅላይ ሚንስትርነት በቁ

የሌበር ፓርቲ ራሱን ችሎ መንግሥት ለማቆም ከሚያስችሉት 326 የምክር ቤት ወንበሮች በላይ ለማሸነፍ በቅቷል።

kier.png

Labour Party leader Keir Starmer hugs his wife Victoria during a post election rally. Credit: AP / Kin Cheung

የሌበር ፓርቲ ከእንግሊዝ 650 የምክር ቤት ወንበሮች 236ቱን በአብላጫ በማሸነፍ ራሱን ችሎ መንግሥት ማቆም የሚያስችሉትን ወንበሮች ያገኘ መሆኑን ቢያረጋግጥም፤ ትናንት ጁላይ 4 በተካሔደው ብሔራዊ ምርጫ እስከ 410 የምክር ቤት ወንበሮችን ጠቅልሎ እንደሚይዝ ተገምቷል።

ውጤቱም ፓርቲውን ለመንግሥትነት፤ መሪውን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት አብቅቷል።

የሌበር ፓርቲ መሪ ኪር ስታርመር፤ ውጤቱን ተከትለው የድል አድራጊነት ንግግራቸውን ባሰሙበት ወቅት "ለውጥ ከአሁን አንስቶ ይጀምራል" ብለዋል።

ድል አድራጊነት አስደሳች ስሜት እንደሚያሳድር ሳይሸሽጉ የተናገሩት ስታርመር፤ አክለውም "የተለወጠው ሌበር ፓርቲ፣ ሀገራችንን ለማገልገል ተሰናድቷል፤ እንግሊዝን መልሶ ከነበረችበት ከፍታ ለማድረስና ሠራተኛውንም ሕዝብ ለማገለገል ዝግጁ ነው።

"እንደ ተለወጠ ሌበር ፓርቲ ዘመቻችንን አካሂደናል፤ እንደ ተለወጠ ሌበር ፓርቲም መንግሥት አቁመን እናስተዳደራለን" ብለዋል።
የቀድሞው የወግ አጥባቂው ፓርቲ መሪና ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በበኩላቸው ድል መነሳታቸውን በፀጋ እንደተቀበሉ በመግለጥ፤ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም መልካም የሥራ ዘመን ተመኝተዋል።

ከሪሺ ሱናክ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ወ/ሮ ሊዝ ትረስን ጨምሮ በደርዘን የሚቆጠሩ የቀድሞው መንግሥት የካቢኔ አባላትና ሚኒስትሮች ወንበሮቻቸውን አጥተዋል።



Share
Published 5 July 2024 5:59pm
Updated 5 July 2024 6:14pm
By Kassahun Seboqa Negewo, NACA
Source: SBS

Share this with family and friends